እወዳለሁ ንጻ ሉቃስ5፥12
<<እወዳለሁ ንጻ>> የሉቃስ ወንጌል 5፥12-16 ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ የጌታ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ ።በዛሬው የወንጌል ጦማር የምናነበው የጌታችንን መለኮታዊ ተአምር ሲሆን ተከትሎም ለሁላችን ስለተደረገልን ታላቅ ውለታ እናጤናለን ፣ ክርስቶስ በምድር ላይ በስጋ የተገለጸው ለሁለት ታላላቅ ምክንያቶች ነው ። 1/ሁላችንን ለማዳን 2/ለዘላለም አርአያነት በስጋ በተገለጠበት የስጋዌው ወራት ህሙማነ ነፍስን {ነፍሳቸው የታመመባቸውን }በትምህርቱ ህሙማነ ስጋን በተአምራቱ በአምላካዊ ሃይሉ እየፈወሰ መድሃኒት ሆኖ መገለጡን በሚያስመሰክር ታላቅነት ለምጻሞችን ሲያነጻ፣ ጎባጣውን ሲያቀና፣እውራንን ሲያበራ፣ሽባዎችን ሲተረትር ፣ ልምሾዎችን ሲያጸና ፣ ሃጢአተኛ ተብለው የተፈረደባቸውን በሰላም ሂድ በሰላም ሂጂ እያለ ሲያሰናብት ፣በአጋንንት ክፉ እስራት ውስጥ ወድቀው የሚማቅቁትን የመቃብር ዳር ምስኪኖች ከስቃይ ሲገላግል ,,,,,,,,,ወዘተ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት በመጽሃፍ ቅዱስ ምስክርነት እናረጋግጣለን ። በፍቅሩ የፍቅር ትርጉም የሆነው ጌታ የእውቀት አስተማሪ ጥበብ አሳማሪ ህግ ሰሪ መሆኑን ለመግለጽ ብዙ ጊዜ አልወሰደም ...