<<< የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም >>>


                 <<< የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም >>>

          ከዚህ በፊት በዚሁ የእግዚአብሄር አሳብ ላይ ባሰፈርኩት ጽሁፍ የተወሰኑ ጉዳዮችን ተመልክተናል ዛሬ ተከታዩን ክፍል እናያለን ። ሶስት መቶ ቀበሮዎችን ሶምሶን ይዞ በጅራታቸው ላይ ችቦ አሰረባቸው እሳት ለኩሶ በጠላት አውድማ ላይ ለቀቃቸው
የታሰረባቸውን እሳት ይዘው ሮጡ ተልእኮዋቸውንም ፈጸሙ ። መሳፍንት 15፥4 ሶስት መቶ ሰራዊት ለእልፍ አእላፍ ጠላት ይበቃል ይህ የሚሆነው ግን ተልእኮው እግዚአብሄር ያለበት ሲሆን ነው ። በመሰረቱ እግዚአብሄር በቁጥር ብዛት አያምንም በሶስት መቶ የጌዴዎን ሰራዊት እንደ አንበጣ እስራኤልን የወረረውን መንጋ እንዳልነበረ አድርጎታል መሳፍንት 7፥1-25 ። ወደ አዲስ ኪዳን እውነትም ስንመጣ ህይወታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለወንጌል አገልግሎት የመረጠው 12ቱን ሃዋርያት ነበረ ከእነርሱም ጋር የተደመሩት 120 የወንጌል እና የአዲስ ኪዳን ቤተሰብ ብቻ ነበሩ ። ዛሬ አለምን የከደነው ወንጌል በነዚህ ጥቂት ሰዎች አገልግሎት 
ተጀምሮ ነው ለሁላችን የተረፈው ። በጥቂቶች ብዙ መስራት ለሚችል የሃይሉ እና የጥበቡ ብዛት ለማይለካ ለእግዚአብሄር ከዘለአለም እስከ ዘለአለም ክብር ይሁን አሜን ። 
       
         የዛሬዋም የከርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ኢያሱስ የጣለባትን የወንጌል አደራ በአግባቡ እንዳትወጣ የወንጌሉንም አላማ የጨበጡ 
አገልጋዮች ለመንገዱ በተፈቀደው ፍጥነት ሮጠው ወንጌልን እንዳያደርሱ ከዲያብሎስና ዲያብሎስ መጠቀሚያ ባደረጋቸው ሰዎች 
ከቁጥር የበዙ ፈተናዎች እና እንቅፋቶች ተኮልኩለው መገኘታቸው በዘመኑ የእግዚአብሄርን ቃል ለማሰር የትናንትና  መልኩን ቀይሮ እየተሰራ ያለ ዘመቻ መሆኑን እና መኖሩን ያሳየናል ።
እንቅፋት የሆኑትን ችግሮች ተቅዋማዊ እና ግለሰባዊ ብለን ከፍለን ለናያቸው እንችላለን ማለትም አስተዳደራዊ ክፍተቶችና ክፋቶች 
ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ በቤ/ክ መዋቅራዊ አሰራር ውስጥ ያሉ ፍትህ እና እውነት የሌላቸው ፍርዶች እግዚአብሄር በየዘመናቱ ለቤ/ክ 
በሚያስነሳቸው አገልጋዮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጥረዋል ነገም ቢሆን የማያዳግም እርምጃ በአስተዳደር ለውጥ ላይ ካልተደረገ ግድያው ስም ማጥፋቱ ልዩነቱ ይቀጥላል ። በሁለት የተለያየ አመለካከት በለቸው ሰዎች መካከል ትክክለኛ ፍርድ እንዲሰጥ 
ሲጠየቅ ለቤ/ከ የሚጠቅም ውሳኔ ሰጥቶ  መምራት ሲገባው መጥረቢያና ቢላዋ በጎን ለሁለቱም እየሰጡ ህዝብና ህዝብ ማህበርና መህበር ሰው ለሰው የሚያጨራርሱ የቤ/ክ ስራ አስፈጻሚዎች ሊመከሩና ስርአት ሊማሩ ያስፈልጋል ።ይህም ቢሆን የእግዚአብሄር ቃል ግን አልታሰረም እይታሰርም ። 
       ግለሰባዊው ስህተትና ችግር ደግሞ የሚያገለግሉትን አምላክ አለማወቅ በድንግዝግዝ ማገልገል ሲሆን እንደ ቅ/ጳውሎስ የቀድሞ ማንነት እግዚአብሄርን ያገለገሉ እየመሰላቸው አንዳንዶቹም ሆን ብለው በስጋ ቅናትና በልብ ክፋት በየስፍራው የሚያስተላልፉአቸው ሃላፊነት የጎደለው መልእክት እና ግንዛቤ ነው  ። ይህ ዛሬም እንቅፋት ነው ።
   ሰይጣናዊው የጠላትነት መረብ ያለተጠላለፈበት ቦታና ሁኔታ የለም እግዚአብሄር አይናችንን ቢከፍትልን መዳን ያለባቸው 
በጌታ ቃል መጎብኘት ያለባቸው ብዙ ነፍሳት ያውም እግዚአብሄር ደማቸውን ከእጃችሁ እቀበላለሁ የሚለን እረኛ እንደሌላቸው 
በጎች በየ ስፍራው የተበተኑ ሁሉ ይታዩን ነበር ። ይሁንና በግለሰቦችና  በራሳችን ድካምም ቢሆን የእግዚአብሄር ቃል አልታሰረም አይታሰርም ።መለኮታዊው ቃል ኪዳን በዘመን ሁሉ ህያው ሆኖ ስለሚኖር ይህ የክብር ወንጌል እስከ አለም ዳርቻ እስከ አለም ፍጻሜ በስልጣን ይሰበካል ምክንያቱም  የእግዚአብሄር ቃል አይታሰርም ።
       ጸሎት >> የመረጥከን የለየከን የክብርህ ወንጌል አገልጋዮች ያደረከን ጌታ ሆይ  ለቃልህ በሃይልና በቅድስና እንድንሰራ
                     በቅዱስ መንፈስህ አግዘን የሰዎችን ሳይሆን ያንተን አሳብ እንድናገለግል በእውነት ቃል ቃኘን ። አሜን ።
ቀ/ትዝታው ሳሙኤል 

Popular posts from this blog

እንዴት እንጹም ?

አስገራሚው የፍቅር ታሪክ