የእግዚአብሄር ቃል አይታሰርም 1
የእግዚአብሄር ቃል አይታሰርም
ክልከላ አልፎ የሚሰማ አዋጅ አልፎ የሚሰራ ከባለስልጣናት በላይ ባለስልጣን የሆነው መለኮታዊውየእግዚአብሄር ቃል ብቻ ነው። ቀድመው የተነሱ መንግስታት ያወጡትን ህግ ቀጥሎ የተነሱት በሚመቻቸው
መንገድ እየቀለበሱ ቀይረውታል ፣ በዘመናችን ደግሞ አንድ አስገራሚ ክስተት አለ ይኸውም ድምጽን በድምጽ
የመሻር መብት የሚባለው ለተወሰኑ ሃያላን ሃገራት የተሰጠ መብት ነው ። ሁኔታው ዘመናዊ የሚመስል ቢሆንም
ከፍትሃዊነት አንጻር ብዙ አከራካሪ ነጥቦችን ማስነሳቱ አልቀረም ።በመሰረቱ የእኔ ነጥብ ምድራዊ ህግ ማብራራት ሳይሆን በምድራዊ ህግ እና በምድራዊ ባለስልጣናት የማይታሰረውን ሰማያዊ ቃል መመስከር ነው ። ስለዚህ አምላካችን እግዚአብሔር በድምጽ የማይሻር ድምጽ ፣ በምድራዊ ህግ የማይቀለበስ ህግ፣ የሰላ አንደበት ባላቸው
ፈላስፎች ቃል የማይረታ ቃል ያለው ንጉስ ነው ። እኛም የምንመራው በዚህ የህይወት ቃል ስለሆነ ስለዚህ ስልጣን
ስላለው ቃል ለነፍሴና ለነፍሳችሁ ለልቤና ለልባችሁ ልጽፍ ወደድኩ።
በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው የክርስትና ህይወት ጉልበታምና በድንቆች የታጀበ ነበረ ፤ መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ የመሰረታት ቤተክርስቲያን ዛሬ ያላትን ነጻነት አግኝታ ከማየታችን በፊት ብዙ መከራዎችን አልፋለች ቤተ ክርስቲያን ስንል የክርስቲያኖችን ህብረት ማለታችን ነው ። ለተቀበሉት የወንጌል አደራ ሲሉ አንገታቸውን ለሰይፍ ሰውነታቸውን ለእሳትና ለአራዊት የሰጡትን ትውልድና ታሪክ በደማቅ ቀለም ከትቦአቸዋል፤የሰው ልጆችን ዋጋ ሁሉ በእጆቹ የያዘው ጌታ ደግሞ ሰማያዊ አክሊልን ደፍቶላቸዋል።፤የዛሬይቱ ቤ/ክ ከክርስቶስ ሰማእትነትን ተምረው በደም የመሰከሩለትን ታማኞች በሻማ ብርሃን እንደ ጌታችን ቀልጠው ማብራታቸውን ትመሰክራለች።
ቅዱስ ጳውሎስ <ይህንን ስለሰበኩ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ ያእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም > 2ኛ ጢሞ 2 ፥ 9 በማለት ወንጌላውያንን በማሰር ወንጌልን ማሰር አገልጋዮችን ከአገልግሎት በማሳደድ እና በመለየት የጌታን ቃል እድገት እና ሁሉን ወራሽነት ማስቆም እንደማይቻል ያረጋግጥልናል ።
የሚገርመው ቅ/ጳውሎስ በቀደመው ማን ነቱ ስሙ ሳውል ግብሩም ክፉ በነበረ ጊዜ ቃሉን የተሸከሙትን እያሳደደ ቢያስርም ቃሉን ግን ማሰር እንዳልቻለ ያኔ ገና አረጋግጦአል ። እስጢፋኖስ ሲወገር እና ሰማእትነት ሲቀበል የወጋሪዎቹን እና የምስክሮቹን ልብስ ከእግሩ ስር አስቀምጦ አሳዛኙን የእስጢፋኖስ ሞት ልቡ በሃዘን እስኪወጋ ቆሞ ተመልክቶአል ። በእስጢፋኖስ ሞት ምክንያት የተበተነው ህዝብም አይሁድ የፈሩትን ወንጌል ይዞ በአለም ተበትኖ ቃሉን በዚያው ልክ አስፋፋው ይህንን እውነት የቅ/ጳውሎስ ልብ አሳምሮ ያውቀዋል ስለዚህ እኛም የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም የሚለውን አዋጅ እናውጃለን ።የዘመናችን የቤ/ክ ፈተናዎች በወንጌል ዙሪያ የሚለውን ደግሞ በመቀጠል እናያለን ,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
ቀ/ትዝታው ሣሙኤል