መንገድ እውነት ሕይወት ዮሐ 14፥6

                    መንገድ እውነት ሕይወት 

                                             ዮሐንስ 14÷6

        ውድ   የዚህ መንፈሳዊ ድህረ ገፅ አንባቢዎች እንደምን ከርማችኋል የጌታ ፀጋና ሰላም ይብዛላችሁ  በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ከላይ የተጠቀሱትን ሶስት ታላላቅ ቃላቶች በተራ ትርጉማቸውን እያየን የመድሃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን  ታላቅ የማዳን ስራ እንመሰክራለን ።
     የዚህ አለም የኢኮኖሚ ተንታኞች ለአንዲት አገር ፈጣን እድገት እና ልማት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው መንገድ እንደሆነ ይስማማሉ ። በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ክፍላተ ሃገራትን እንዲሁም ከአዋሳኝ አገራት ጋር የንግድ የባሕል የኢኮኖሚ ልውውጦችን ለማድረግ ጉልህ ድርሻ የሚወጣው መንገድ እንደሆነ ያረጋግጣሉ
ሃሳቡ ከእውነት ያልራቀ ስለሆነ እኛንም ያሳምነናል ። በሃይማኖታዊ እይታም መሰረት መንገድ ብዙ ሚስጥራትን የያዘ ቃል ነው ስለዚህ የዚህ ዓለም ጠበብቶች የተስማሙበትን የመንገድን አስፈላጊነት ማለትም በድንጋይ ወይም ዘመናዊው አስፋልት አልያም የጥርጊያ መንገድ ሁሉም እንደየአቅማቸው
ለህብረተሰቡ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት እኛ ልንለው የምንችለውን ፈርጥ እውነት ከፍ አድርገን እናሳያለን ።

                    መንገድ 1/ ኢየሱስ የህይወታችን መንገድ ነው ።

 ከምድራዊ መንደር ከስጋዊ አመለካከት ከስህተት ከተማ እግራችንን ነቅለን ወደ ሰማይ መንግስት ወደ ዘለዓለም መንግስቱ የምንጘዘው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ መንገድነት ነው ። ኢየሱስ ከምድር እስከ ሰማይ የተዘረጋ የህይወት መንገድ ነው ። እንቅፋት የሌለበት ጨለማ የማይዘጋው የሚጘዙበትን ሁሉ ወደ ታላቁ ክብር የሚያደርስ መንገድ ነው ።መንገዳችን ማን ነው ? መንገዳችን ስንት አይነት ነው ? መንገዳችን ምን አይነት ምልክቶችን ይዟል ? እነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ ካልተመለሱ ያለንበትን ስፍራ በውሉ መረዳት አንችልም  ወደየት እንደምንሄድም አናውቅም አንድ መንደደኛ ከቤቱ ሲወጣ መነሻውን እና መድረሻውን በትክክል እርግጠኛ መሆን ይገባዋል ። ክርስቲያኖች ወደ አብ የሚያደርስ አንድ መንገድ አለ እርሱም ኢየሱስ ነው ። የመንገዱ ምልክቶች ፍቅር፣ምህረት፣ ይቅርታ፣ቅንነት የመሳሰሉት ናቸው ።ወልድን ያላወቀ ወይም ወልድ ካልገለጠለት በስተቀር አብን የሚያውቅ የለም
ማቴ 11፥27 ስለዚህ ያላየነውን አብን መንፈስ ቅዱስን በአጠቃላይ ታላቁን አምላካዊና መለኮታዊ ምስጢር የተረዳነው የምንረዳው በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስናምን እን በእርሱ መንገድነት ብቻ ስንራመድ ነው ።
    መንገዱን ተጉዞ የጨረሰ የመጨረሻዋን መስመር ሲሻገር አንድ ልዩ ስጦታና ሽልማት ተዘጋጅቶ ይጠብቀዋል ያም ስጦታ ዘለአለማዊው የክርስቶስ መንግስት ነው ። ክርስቲያን መጨረሻውን የሚያውቅ የግብና የአላማ ሰው ነው በደሙ ዋጋ ከፍሎ በሞቱ ያስታረቀንና የታረቀን ስለሚወደን የዘለአለም መንግስቱን ርስት አድርጎ ሊሰጠን ነው ። በክርስትና ህይወት መንገድ በድል አድራጊዎች ሰልፍ ውስጥ
ትርጉም ያለውን የህይወት ጉዞ ከጀመሩ በሗላ የዚህ ዓለም ጩኸት ውበት እና ፈንጠዚያ ስቦአቸው
መንገድ የሚቀይሩ ከመስመሩ ወጥተው ዓላማቸውን ዘንግተው ወደ ዘለዓለም ሞት የሚፋጠኑ ብዙዎች ናቸው ። በሃገር አቛራጭ የሩጫ ውድድር ውስጥ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች በሙሉ ከተከለለው የሩጫ መስመር ሳይወጡ ውድድራቸውን የመጨረስ ግዴታ አለባቸው በከተማ እና በቀለበት መንገዶች ላይም
መኪና የሚያሽከረክሩ ሹፌሮችም በየመንገዱ ዳር የተሰቀሉትን የፍጥነት መጠን እና የመንገድ ህጎች በማክበር ማሽከርከር አለባቸው ። በክርስቶስ መንገድነት ስንጓዝም በህያው ቃሉ የተደነገጉልን ልዩ ልዩ
ክርስቲያናዊ ህጎች አሉ ለምሳሌ ፦ሌሎችን መንገደኞች በፍቅር እና በጥንቃቄ ማየት፣ የደከሙትን ማጋዝ ፣ ነዳጅ እንደጨረሰ መኪና እምነትና መንፈሳዊ ሃይል አጥተው የቆሙትን በቃሉና በጸሎት እየረዱ እንዲራመዱ መርዳት ፣ አደጋ ላለማድረስ አስተውሎ መጓዝ ፣ ቀይ መብራቶችን /ከእግዚአብሔር ጋር ሊያጣሉን የሚችሉ ሆነው የተከለከልናቸውን ነገሮች ጥሶ አለማለፍ / ,,,,,,,,,,, ወዘተ የመሳሰሉ ድንጋጌዎችን በማከናወን ለራሳችንም ለሌሎችም በማሰብ የምንጓዝበት የህይወት መንገድ ነው ።መንገዱ ኤግዚት/EXIT/ የለውም ቅዱስ ጴጥሮስ <ካንተ ወደማን እንሄዳለን > እንዳለው ቀጥተኛውና ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ አመራጭ የሌለው መሄጃችን ነው ክብር ምስጋና ጌትነት አምልኮ ለእርሱ ይሁን
ከአባቱ ጋራ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ ዛሬም ለዘለዓለም አሜን ።ይቀጥላል
     ቀሲስ ትዝታው ሳሙኤል ።

               እውነት 2/ኢየሱስ የዘለአለም እውነት ነው ።         


Popular posts from this blog

እንዴት እንጹም ?

አስገራሚው የፍቅር ታሪክ