አስገራሚው የፍቅር ታሪክ
አስገራሚው የፍቅር ታሪክ
በመጀመሪያ እግዚአብሄር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ስማይና ምድር ሲፈጠሩ አሁን በሰማይና በምድር ውስጥ ያሉት ፍጥረታት በሙሉ በእግዚአብሄር ቃል ሆኑ ፍጥረትን ሁሉ አስቦ በቃሉ የፈጠረው አምላክ
በራሱ አርአያ እና አምሳል አዳምን ከአፈር አበጀው የህይወት እስትንፋስን
በአፍንጫው እፍ አለበት ህያውም ሆነ የህይወት መመርያ ተሰጠው
የተሰጠውን ነጻነት ተጠቅሞ የቀረበለትን ምርጫ ከህይወት አጋሩ ከሄዋን ጋር
ተስማምቶ ሞትን መረጠ የእግዚአብሄርም ቅን ፍርድ በላዩ ወደቀበት ስለዚህ ልጅነቱን ጸጋውን ክብሩን ስልጣኑን ተቀማ ።
ይህ ታሪካዊ ስህተት የሰው ልጆችን ነጻነት ጠቅልሎ አስሮ በመቃብር
የቀበረ የአለማችንን መልክ የህይወታችንን ውበት በሞት ጥላሸት ለቅልቆ ያበላሸ በመጀመሪያው ንጹህ ታሪካችን ላይ ጠባሳ የጣለ ክስተት ነበር ።
በሄዋን ማህጸን በአዳም አብራክ ውስጥ ሆነን ሁላችንም ተረገምን፣የሞትን
ፍርድ ተቀበልን ። ቅ/ጳውሎስ ይህንን ሲያብራራ < ስለዚህ ምክንያትሃጢአት በአንድ ሰው ወደ አለም ገባ በሃጢአትም ሞት እንደዚሁም ሁሉ ሃጢአትን ስለደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ ።> ሮሜ 5፥12 ይህ መጽሃፍ ቅዱሳዊ ቃል
እንደሚያስረዳን በዘር እየተላለፈ ትውልድን ሲጨርስ የነበረው ሞት መንስኤው የአዳም በደል እንደሆነ በተጨማሪም ቀጥሎ የተፈጠረው ትውልድም በሃጢአት ባህር ውስጥ የተነከረ ማንነት ስለነበረው ከፍርድ እና
ከሞት ሊያመልጥ እንዳለቻለ ነው ።
ስለዚህም ኪሳራ እና ውድቀት ብዙ ነቢያት አልቅሰዋል ብዙ ደም ፈስሶአል
እጣን፣እንባ፣ጾም፣ጸሎት ፣ሱባኤ፣መስዋእት,,,,,,ወዘተ የሰው ልጆች ሁሉ ይህንን አስከፊ ሁኔታ ይለውጣል ብለው ያመኑበትን ሃይማኖታዊ ስርአት ሲፈጽሙ ሲደክሙ ኖረዋል ነገርግን የይስሃቅ ቤዛ ሆኖ በእጸሳቤቅ ታስሮ በምሳሌ የተገለጸው አማናዊው በግ የእግዚአብሄር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይመጣ ፍጹማን ሊሆኑ ስለማይችሉ የመሲሁን መገለጥ እስከመጨረሻው
መጠበቅ ነበረባቸው ። ይህንን ናፍቆታቸውን በትንቢታቸው በዝማሬአቸው
ሲገለጹት ነበር <ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ ተራሮች ምነው ቢናወጡ,,,,,,ሁላችን እንደርኩስ ሰው ሆነናል ጽድቃችንም እንደ መርገም ጨርቅ ነው ,,,> ኢሳ 64፥1-7 መዝሙረኛው ዳዊትም <መቼ ታጽናናኛለህ
እያልኩ አይኖቼ ስለ ተስፋ ቃልህ ፈዘዙ >መዝ 119፥82 በማለት ሲጮሁ እናያለን ።
ይህ የፍጥረት ሁሉ ናፍቆት የሆነው ጌታ ኢየሱስ ጊዜ ቆጥሮ ከብዙ ምህረቱና ይቅርታው ከፍቅሩ ጋራ ከሰማያት ወረደ ከንጽህት ድንግል ማርያም ተወለደ /ገላ4፥4/ በማህጸን የጀመረውን የካሳ ስራ በመስቀል ሞት
እስኪደመድመው ድረስ በብዙ አስቸጋሪ የህይወት ፈተናዎች ውስጥ አለፈ
ክርስቶስ ለምን ወደዚህ አለም እንደመጣ ያውቃል አላማው እኔንና አንተን
አንቺን ፍጥረትን ሁሉ ማዳን ነው ለዚህ ደግሞ መከፈል ያለበትን ዋጋ ሁሉ ሊከፍልልን ተዘጋጅቶ ስለመጣ መከራውን በፍቅር ታገሰ ደሙ እንደ ውሃ መሬቱን አራሰው ስጋው በግፈኞች ጅራፍ አልቆ ነጭ አጥንቶቹ እስኪቆጠሩ
ከዚያ በፊት ባልሆነ ከዚያም ወዲህ የማይሆን ግፍና መከራ ስቃይ ተቀበለ
የጌታን መከራ ይገልጻሉ ተብለው የተዘጋጁ ትንንሽና ትልልቅ ጥራዝ ያላቸው መጻህፍት በአምስት ስንኞች የተቀመሩ መዝሙሮች የሆልዩድ እና የአውሮጳ ፊልሞች ባለቅኔዎች ባለዜማዎች ሁሉም በገባቸው መጠን መከራውን አካፈሉን አስለቀሱን አስቆዘሙን ግን አንድ ነገር የማልደብቃችሁ
የተባለውም የተሰራውም በቂ እንዳልሆነ ነው ስቃዩ ከተነገረን በላይ ነውና።
ከሰማናቸው አስገራሚ ካልናቸው ብዙ ምድራዊ የፍቅር ታሪኮች በላይ ተወዳዳሪ የሌለው የኢየሱስ ፍቅር ነው የወደደን መለካምነት ኖሮን ሳይሆን
እንዲያውም ጠላቶቹ ሳለን እንዲሁ በነጻ አፈቀረን በሚያርዱት ፊት አፉን ያልከፈተ በግ የሁላችን ህይወት ክርስቶስ ነው ።
እኛ ሁላችን ስለፍቅር ማውራት የማንችል ኮልታፎች ነበርን አንደበታችን
ዳዴ እንደሚል ህጻን የሚድህ ነበረ ፍቅር ምን ማለት እንደሆነ ትምህርቱን
በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር አሳየን ደሙን ቀለም አጥንቱን ብእር ስጋውን
ብራና አድርጎ ፍቅር የሚባለውን መለኮታዊ ታላቅ ምስጢር አድምቆ ጻፈልን
ስለዚህ ክርስቶስ ፍቅር አስተማሪ ብቻ ሳይሆን ራሱ ፍቅር ነው ።
ውድ አንባብያን በዚህ አስገራሚ የፍቅር ታሪክ ተገርመን ተደንቀን ንባቡን እንድናቆም አልፈልግም የሚገረም እና አድናቂ ክርስቲያን መሆን አይገባም
ወደዚህ የፍቅር ብርሃን ውስጥ እንድንገባ እኛም እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ሁሉን መውደድ የምንችልበትን ፍቅር በውስጣችን ማሳደግ እንዳለብን ልናውቅ ይገባል ግብዝነት በሌለው ፍቅር እርስ በእርሳችን እንዋደድ እንጸልይ እንበርታ ። የእግዚአብሄር ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን።አሜን
ቀሲስ ትዝታው ሣሙኤል