ኒቆዲሞስ



                        መክሊት

              የጽሁፌ መነሻ ማቴ 25፥14-23  ነው ። መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በምሳሌ  ስለ መንግስተ ሰማያት  ካስተማረው ትምህርት በጠቀስነው ጥቅስ ውስጥ ተደጋግሞ የተነገረውን ቃል በምሳሌነት ይዘናል  <መክሊት >  አፌን በምሳሌ እከፍታለው  መዝ  77 እንዳለው መዝሙረኛው ጌታችንም ለሚከተሉት ሁሉ  ለነጋዴው በንግዱ ስርአትና በገንዘብ ፣ለገበሬው በእርሻና በዘር ፣ ለቤት እመቤቶች /ለሴቶች / በቡኮና በእርሾእየመሰለያስተምር ነበር  ።

       የባሮቹ ጌታ ወይም ንጉስ ወደሩቅ ሃገር ሊሄድ ሲል ባሮቹን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ፣ለሁለተኛው ሁለት መክሊት ፣ለሶስተኛው  አንድ መክሊት ሰጣቸውና እስክመጣድረስ ሰርታችሁ አትርፋችሁ ጠብቁኝ ብሎ ጥብቅ አደራ ሰጥቶአቸው  ሄደ ይላል ታሪካዊው ምሳሌ ።

  ውድ የእግዚአብሄር  ልጆች ንጉሳችን ክርስቶስ በስጋ ማርያም ተገልጦ በምድር ላይ ማድራዊ ብቻ ሆነን እንድንቀር ያደረገንን በደም በውርስ ከእርግማን በታች ያደረገንን ዘለአለማዊ ሞት በሞቱ ደምስሶልን አዲስ የህይወት ምእራፍ ከፍቶልናል ። ታዲያ ይህንን ለሁላችን የሚሆን የመዳን ጸጋ ያለ አድልዎ ባጎናጸፈን ጊዜ የክርስትናን የእውነተኛውን  ሃይማኖት አደራ ሰዎች ሁሉ የሚድኑበትን ወንጌል በተለይም ለመቶ ሃያው ቤተሰብ አደራ ሰጥቶ አትርፋችሁ ጠብቁኝ ብሎ ነው ወደ አባቱ ያረገው ።በዚህ ምልከታ መሰረት ሁላችንም የተቀበለነው በእኩልነት የሚያመሳስለንና የሚያስጠይቀን መክሊት አለ ።

           አንደኛው መክሊታችን እግዚአብሄር አብ ለሞት እንካን ሳይሰስት የሰጠን የባህሪ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።  ኢየሱስ መክሊታችን ነው በእርሱ የዘላለም ህይወትን እናተርፋለን አትርፈናልም ፣በእርሱ ከዘለአለም ሞት ተርፈናል ፣ፍቅርን ፣ምህረትን ፣ ይቅርታን አትርፈናል ክርስቶስን ባናምን ይህ ሁሉ የለንም ። ዘሬም በመንፈሳዊ እና በስጋዊ ህይወት ኪሳራ ላይ ያሉ ሁሉ ሊቀበሉት የሚገባ አንድ እውነት መናገር እፈልጋለው ፤ ከክርስቶስ ጋር ካልሰራችሁ አንዳች አታተርፉም ትዳራቸውን ፣ኑሮአቸውን ውጫቸውን ውስጣቸውን  በአጠቃላይ ሁለንተናቸውን ሳይሰጡ  ለውድቀታቸውና ለኪሳራቸው አሁንም የሞተላቸውን ጌታ የሚከስሱ አሉ  ወገኖቼ ማትረፊያ መክሊታችሁን ኢየሱስን አጥብቃችሁ ያዙ።<<ሰው አለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል >> ማቴ 16፥25

   የክርስቶስ  ወንጌል መክሊታችን ነው ። መከሩ ብዙ ሰራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው ብሎ ጌታ እንደተናገረው  የአለምን ህዝብ በወንጌል ለመድረስ በዚህ ጉዳይ ጸጋና አላፊነት ከተሰጣቸው ሃዋርያት ጀምሮ በየዘመኑ የሚነሳው ትውልድ በሙሉ መክሊቱ ወንጌልን ተቀብሎ ለመንግስተ ሰማያት ትርፍ መስራት አለበት ። ለሃዋርያት የተሰጠውን አደራ ማቴ 28፥16 እና ዮሐ  20፥15  አህዛብን ሁሉ በወንጌል እውነት እንዲያሳምኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ስልጣንን ሰጥቶአቸዋል ። እነርሱም የተቀበሉትን  መክሊት በእልፍ አእላፋት ትርፍ አትርፈው ለእኛም ተርፈዋል ።ግልገሎችን ፣ጠቦቶችን ፣ በጎችን ወይም ህጻናትን'ወጣቶችን እና አዛውንትን ልሁሉም በክርስቶስ አሳብ አገልግለው አደራቸውን ተወጥተዋል ።

    ውድ ክርስቲያኖች በዘመናችን ያለውን የክርስትና ህይወት ክርስቶስ ከሰጠን መክሊቶች ጋራ አነጻጽረን ስንመለከት ምን ያህል እዳ ፣ሃላፊነት  እንዳለብን እንረዳለን ይህንን ነጥብ በሶስት ከፍለን እንመለከታለን ፤   

      አንደኛ-  በቤተ ክርስቲያን = ቤተ ክርስቶያን ለእያንዳንዳችን የተሰጠችን መክሊታችን ናት በውስጥዋም ስንኖር በተስጡን ጸጋዎች በቅንነት በመታዘዝ በፈሪሃ እግዚአብሔር ለናገለግል ይገባል ። የተሰጣቸውን መንፈሳዊ ጸጋዎች ሳይጠቀሙበት ብዙ መስራት ሲችሉ እጃቸውን ሰብስበው በርቀት ቆመው የሚመለከቱ ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም  አንዳንዱ ስም ይወጣለኛል ፣ መከራ ይደርስብኛል I፣የግል ስራዬን እና ቤተ ሰቤን  ያስረሳኛል በሚል ፍራቻ ከመንፈሳዊ ግዴታ ውጪ የሆኑ አሉ አንድ መክሊት ተቀብሎ እንደቀበረው ክፉ ባርያ መክሊቱን የሰጣቸው ተመልሶ ሲመጣ የሚመልሱት እንዳያጡ ዛሬ ተግተው መስራት እንዳለባቸው ሳልጠቁም አላልፍም ።ከዚህምጋር አምስት መክሊት ተቀብለው ሌላ አምስት  ያተረፉ ባለሁለትም ትርፍ ያላቸው  የቤተክርስቲያን እንቁዎች ብዙ ናቸው የነዚህን ትጉሃን በረከት ያሳድርብን ።

      ሁለተኛ = በቤተሰባችን = ትዳራችን እና ልጆቻችን መክሊቶቻችን ናቸው  የተሰጣችውን ትዳር በጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ የበተኑ ልጆቻቸውንn በጸሎትና በመንፈሳዊ እውነት በጥንቃቄ ማሳደግ ተስኖአቸው በሱስ ፣ በበሽታ ፣ በወንጀል አልፎም በሞት የተነጠቁ ሰዎች ሚስት በባል ባል ደግሞ በሚስት ወይም በልጆች ያሳብባሉ እንጂ መክሊታቸውን ስለልሰሩበት የመቅበራቸው ውጤት ነው ።የጎዳና ተዳዳሪዎች ፣ ሴተኛ አዳሪዎች ፣ ቤትና መኪና ሰብረው የሚዘርፉ በስለት ወግተው ስው የሚገድሉ ለህዝብና ለመንግስት ያስቸገሩ የምድራችን ጉዶች ትዳርና ልጅ ከጌታ የተቀበሉት መክሊት መሆኑን ባልተገነዘቡ ወላጆች ምክንያት የደረሰብን ኪሳራ ነው ። ወላጆች ሆይ ስላፈራችሁት ፍሬ ስለ ልጆቻችሁ ስለ ሚቀጥለው ትውልድ ጸልዩ። እግዚአብሔር ያስበን ። 

     ሶስተኛው = በግል ህይወታችን =   መጽሃፍ ቅዱስ<< የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ>>  ያላል ፊልጵስዮስ  2፥12  ሰው የገዛ ህይወቱን ክርስቶስን በማመን እና ንስሃ በመግባት ማትረፍ አለበት ።ህይወታችን  ከእግዚአብሔር የተቀበልናት  መክሊታችን ናት ግለሰባዊ ማንነታችን ብቻ ነው በእግዚአብሄር ፊት ሊያስቀጣንም ሊያስመሰግንም የሚችለው ። ዘፍጥረት 19፥17 <<ራስህን አድን ወደ ኅላህ አትመልከት >> በቤተሰብህ እምነት እና ሃይማኖት አትድንም የሎጥ ሚስት ለዚህ ትክክለኛ ማሳያ ነት መመሪያውን ትታ ወደ ከተማው ስትዞር የጨው ሃውልት ሆና ቀረች ያመኑትና ያልዞሩት ሎጥና ልጆቹ  ለብቻቸው ተሻግረዋል  ስለዚህ ወዳጄ ነፍስህን መክሊትህን አትርፍ ራስህን አድን ።ማጠቃለያ = ሌላ ከእግዚአብሄር መዳፍ የተቀበልናቸው ብዙ መክሊቶች አሉ ለምሳሌ ጤናችን ፣ ያፈራነው ሃብት ፣እውቀታችን ፣ ሰላማችን ፣ ተሰሚነታችን እና ሰሚነታችን >>>>>>>> ወዘተ ለእግዚአብሄር መንግስት ለክርስቶስ ክብር  ልንሰራባቸው የተሰጡን ናቸው ። በመክሊታችን ሰርተንበት አደራየሰጠን የሁላችን ጌታና ንጉስ ሲገለጥ ክብርና ደስታ እንዲሆንልን እግዚአብሄር ይርዳን ።

ጸሎት = አባቴ እና አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስ  ሆይ  በመገለጥህ ጊዜ በፊትህ የማቀርበው የህይወት ትርፍ እንዳላጣ ብጠብቀኝ የሰጠከኝንም  መክሊቶች  በትክክል እንድሰራባቸው እርዳኝ ።አሜን

Popular posts from this blog

እንዴት እንጹም ?

አስገራሚው የፍቅር ታሪክ