ትንሳኤ


        " ተነስቷል "

   የተናገረውን የሚያደርግ የማያደርገውን የማይናገር በቃልም በግብርም የታመነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀድሞ በገነት የሳተውን አዳምን እና በአዳም ውድቀት የወደቅነውን እኛ ሁላችንን ያጣናትን ሰማያዊት አገራችንን ሊመልስልን ከገባንበት ጨለማና ፍርድ ሊቤዠን የተናገራትን ቀን ቆጥሮ ተገለጠልን ።

 በነገራችን ላይ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ለመሞት ነው ። ደም ሳይፈስስ ሰርየት የለም እንዳለው መጽሃፍ የእንስሳት እና የሰዎች ደም በክርስቶስ የመጣውን ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጣ ስላልቻለ ደግሞም ስለማይችል በመስቀል ላይ ሃጢአታችንን ሊሸከም ፣ሞቶ ሞትን ሊገድል ፣በትንሳኤውም ዘለዓለማዊነታችንን ሊያረጋግጥልን በኩር ሆነልን ።
    ስለዚህ የመጣበትን አላማ ስለሚያውቅ ብዙ ውርደት በትህትና ተቀበለ ብዙ ስቃይ በዝምታ አስተናገደ መከራውን ሳይሆን በመከራው የምንተርፈውን የእኛን መዳን እያየ ተፅናና በችንካር እያማጠ ዳግመኛ ከማይጠፋ ዘር  ወለደን።
     በሚያስተምርበት ወቅት ይህንን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሶስተኛውም ቀን አነሳዋለሁ እንዳለው ሶስት ቀንና ሶስት ሌሊት በምድር ውስጥ አሳልፎ በሶስተኛው ቀን የሞትን ሃይል አድቅቆ የመቃብርን ህግ ሽሮ ዳግም በማይሞት ማንነት እና አካል በተዘጋ መቃብር ኢየሱስ ተነሳ። ክብር ምስጋና ኃይልና ስልጣን ሁሉ ለእርሱ ይሁን አሜን ። 
  ውድ አንባቢ ሆይ ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋራ ከተባበርን ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ እርሱን እንመሰለዋለን ሞት የማይቀር እዳ ሆኖ ብንሞትም መነሳታችን ግን አይቀርም በመሬት ላይ የተዘራ የስንዴ ቅንጣት መጀመሪያ ይበሰብሳል ከዚያ መብቀል ይጀምራል በኋላም ብዙ ፍሬ ያፈራል እኛም ስጋችን በመሬት ተቀብሮ ፈርሰን በስብሰን አንቀርም በአዲስ ማንነት በማይሞት ሰውነት እንደ በኩራችን እንደ ኢየሱስ እንነሳለን የዘለአለምን ህይወትም እንወርሳለን ።
    ውድ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ያገኘነው ስጦታ ከቁጥር ብዙ ስለሆነ ጌታ ሁለንተናችን ነው ብንል ይቀለናል ። ትንሳኤውን በገንዘብ ሃይል ለመደበቅ የተደረገው የአይሁድ ጥረት በእውነት ሃይል ከሽፏል እኔም አንተም አንቺም የዚህ ታላቅ እውነት ምስክሮች ነን እንደተናገረው ክርስቶስ ተነስቷል በልባችን ያመንነውን በአንደበታችን መስክረን እንድንድንና እንድንፀድቅ እግዚአብሔር ይርዳን አሜን ።
      ቀሲስ ትዝታው ሣሙኤል 

Popular posts from this blog

እንዴት እንጹም ?

አስገራሚው የፍቅር ታሪክ