የፍቅርህ እሳት /ጸሎት/
የፍቅርህ እሳት
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ » የፍቅርህ እሳት ይነድዳል በየዘመናቱም አዲስ ነውና ሙቀት ያላገኙትን በሃጢአት ቅዝቃዜ በቂምና በበቀል ብርድ የሚንዘፈዘፉትን ነፍሳት በህያው ሙቀቱ ከልብና ከህሊና ሞት ይታደጋል ።
መድሃኒቴ ሆይ » ፍቅር የሚለውን ታላቅ እውነት የተማርኩት ካንተው ነው ። ጥርስ ያወለቀ ጥርሱ እንዲወልቅ አይን ያጠፋ አይኑ እንዲጠፋ በታወጀበት አለም ምህረትና ይቅርታ መውደድና ማፍቀር ሰማእትነት እና ፍጹምነት ከባህሪህ አውጥተህ ስላሳየከኝ ባንተ የነበረው አሳብ በእኔም እንዲኖር ስላበረታከኝ ሁሉን ባንተ ስለተማርኩኝ መውደድን መወደድን ያየሁብህ ወዳጄ አመሰግንሃለው ።
አለሙን አንድ ያደረግከው ሆይ» ላንተ መገዛቴ በሙሉ ሃይሌ እና ጉልበቴ ነው ።
ደምህ የሃጢአቴን ብዛት ጠርጎ አስወግዶልኛል ቁስልህ የነፍሴን ቁስል ፈውሶልኛል
ጥምህ የነፍስ ጥሜን ቆርጦልኛል መራብህ የዘለአለም ርሃቤን አስወግዶልኛል የሆንክልኝ ሁሉ ከቃላት በላይ ነው ባወራም ብናገርም ማለቂያ የለውም ።
ሰላሜ ሆይ » የነበረህን ያንን ሁሉ ክብር ትተህ እንደ ምስኪን ደሃ ማደሪያ እንደሌለው መንገደኛ ተንከራትተህ በቤትህ ያሉትን ዘጠና ዘጠኙን ሰራዊትህን ትተህ
በአባትነት ፍለጋህ ያገኘከኝ የማርከኝ የመንግስትህ ዜጋ ያደረከኝ አንተ ለእኔ የዘለአለም መኖሪያዬ ነህ መጠጊያዬና አምባዬ ነህ ።
ውዴ» እንደምወድህ አንተው ታውቃለህ ለእኔ ደስታ እንደደከምክ በድካም እንዳስደስትህ እተጋለሁ የከፈልክልኝን ውድ ዋጋ እያሰብኩ ውድ ህይወቴን ላንተ ብቻ
አስገዛለው እሰግድለሃለው እዘምርልሃለው ቃልህን እሰማለው ፍለጋህን እከተላለው
ካንተ ወደማንም ስለማልሄድ ካንተጋር እኖራለሁ ።
ወዳጄ ሆይ » ቃልህን እንድኖርበት እርዳኝ ዛሬ ከምወድድህ በላይ እንድወድህ
የፍቅርህ እሳት በልቤ ይቀጣጠል ። አሜን ።
የህማማት ጸሎቴ , ቀሲስ ትዝታው ሣሙኤል።