እወዳለሁ ንጻ ሉቃስ5፥12


                       <<እወዳለሁ ንጻ>>

                          የሉቃስ ወንጌል 5፥12-16 
       ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ የጌታ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ ።በዛሬው የወንጌል ጦማር የምናነበው የጌታችንን መለኮታዊ ተአምር  ሲሆን ተከትሎም ለሁላችን ስለተደረገልን ታላቅ ውለታ እናጤናለን ፣
     ክርስቶስ በምድር ላይ በስጋ የተገለጸው ለሁለት ታላላቅ  ምክንያቶች ነው ። 
1/ሁላችንን ለማዳን     2/ለዘላለም አርአያነት  በስጋ በተገለጠበት የስጋዌው ወራት ህሙማነ ነፍስን {ነፍሳቸው የታመመባቸውን }በትምህርቱ  ህሙማነ ስጋን በተአምራቱ በአምላካዊ ሃይሉ እየፈወሰ
መድሃኒት ሆኖ መገለጡን በሚያስመሰክር ታላቅነት ለምጻሞችን ሲያነጻ፣ ጎባጣውን ሲያቀና፣እውራንን
ሲያበራ፣ሽባዎችን ሲተረትር ፣ ልምሾዎችን ሲያጸና ፣ ሃጢአተኛ ተብለው የተፈረደባቸውን በሰላም ሂድ
በሰላም ሂጂ እያለ ሲያሰናብት ፣በአጋንንት ክፉ እስራት ውስጥ ወድቀው የሚማቅቁትን የመቃብር ዳር ምስኪኖች ከስቃይ ሲገላግል ,,,,,,,,,ወዘተ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት በመጽሃፍ ቅዱስ ምስክርነት እናረጋግጣለን ። 
       በፍቅሩ የፍቅር ትርጉም የሆነው ጌታ የእውቀት አስተማሪ ጥበብ አሳማሪ ህግ ሰሪ መሆኑን ለመግለጽ ብዙ ጊዜ አልወሰደም ቃል አውጥቶ ያስተማረበት ዘመን ከሶስት አመታት በጥቂቱ የዘለለ ሲሆን በተግባር ያሳየን ትህትናው ፣ትእግስቱ፣ፍቅሩ፣ታዛዥነቱ ፣ዝምታው,,,,, በአጠቃላይ ዮሐንስ በወንጌሉ ቢጻፍና ቢዘረዘር ሰማይና ምድር የማይበቃው ነው ባለው አሳማኝ ስራው ከሰላሳ አመታት በላይ ሰፍቶ እናየዋለን ደግ መምህር ስለሆነ በተግባር ያስተማረን በልጧል አርአያነቱም ጎልቶ ይታያል ።
<ከመጠምጠም መማር ይቅደም ፤ በምላስ ከመሾም ዝምታ ይቅደም > አንዳንድ አስተዋዮች ለሰው አንድ ምላስ እና ሁለት ጆሮ የተሰጠው ብዙ እንዲሰማ ጥቂት እንዲናገር ነው ይላሉ እኔም እስማማለሁ።
ከምንናገረው ብርቱ ንግግር ይልቅ የምንተገብረው ጥቂት መልካምነት ሃይል ኖሮት የሰውን ልብ ይቀይራልና በስራ እንድንገለጥ መንፈስ ቅዱስ ይርዳን።
          ሰውዬው ከእራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ መላው ሰውነቱ በለምጽ በሽታ የነደደ ሰው ነበር
ሉቃስ በወንጌሉ እንደተረከልን ለጻድቃን ሳይሆን ለሃጢአተኞች ለጤነኞች ሳይሆን ለህመምተኞች እረፍትና መዳን እንደመጣ የሰሙና ያመኑ ሁሉ ከስጋ ደዌያቸው ከመንፈስ ሸክማቸው ለመገላገል ወደእረፍት ውሃ ወደህይወት ምንጭ ኢየሱስ ክርስቶስ ይተምሙ ነበር ይህም በለምጽ በሽታ የተጠቃ ሰው ቀርቦ «ጌታ ሆይ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ » አለው በዚህ ንግግር ውስጥ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ጥንካሬዎችን እና በኛም ህይወት ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸውን የእምነት መስፈርቶች ያስተምረናል
      » ብትወድስ  ማለቱ እንድድን ወድደህ ብትፈቅድልኝ ማለቱ ነው ይኸውም መዳን በአምላካችን ፈቃድ ስለሆነ በጸሎታችን ውስጥ ጌታ ሆይ መዳኔን ውደድልኝ መፈወሴን ፍቀድልኝ ብሎ መጸለይ የአማኝ ስርአት ነውና «ምህረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ»
ሮሜ9፥16 እንዳለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምህረትና ይቅርታ በእግዚአብሔር ፈቃድ መሰረት ነው።
      » ልታነጻኝ ትችላለህ የሚለው ቃል የእምነት ቃል ነው ። የክርስቶስን ሁሉን ቻይነት በሚያምን  ልብ የተመሰከረ ታላቅ ምስክርነት ነው ። ጸሎታችን ልመናችን ሁሉ የሚፈጸምልን በእምነት የጌታን ሁሉን ቻይነት ስናውጅ ነው ኢዮብ በጸሎቱ «ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንክ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አሁን አወቅሁ» ኢዮብ 42፥2 ፤ ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ትችላለህ ብትወድድ ብትፈቅድ ይህንን አድርግልኝ ይህንን ፈጽምልኝ እኔ የምፈልገው ይህንን ነው ነገር ግን ያንተ ፈቃድ ይሁን ልንለው ይገባል ።ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻለምና።
      ወገኖቼ የለምጽ በሽታ በሙሴ ህግና ስርአት መሰረት ምንያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ ኦሪት ዘሌዋውያን ምእራፍ 14 እና 15 ብታነብቡ ሰፊ ግንዛቤ ታገኛላችሁ ርኩሰት ተብሎ የሚጠራ የሃጢአተኝነት ምልክት ነበረ መድሃኒታችን የመጣው ለሁላችን ድህነት ስለሆነ የዚህን ሰው ጸሎት እና ልመና ሰምቶ ሊምረው ወደደ ስለዚህም ለጽሁፋችን መነሻ የሆነውን የድህነት ቃል ተናገረ
«እወዳለሁ ንጻ» አለው ያ ምስኪን ሰው ከበሽታው ጋር ለብዙ ዘመን የሰዎችን ስድብና ንቀት እያየ ሲሰቃይ ቢኖርም ዛሬ ግን ሳይጸየፍ የሚቀርበው ስድቡን የሚሰደብለት ሞቱን የሚሞትለት በደም ዋጋ የሚቤዠው ጌታ መጥቷልና በጌታ ቃል መሰረት ከለምጽ በሽታው ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ነጻ ፈነጠዘ ዘለለ ነጻ ላወጣው ንጉስ ተምበረከከ ክብር ሰጠ ። ክብርና ምስጋና ሰማይና ምድርን ለገዛው ለሚገዛው ስሙ ይሁን አሜን ።
      « እወዳለሁ ንጻ » የሚለው የመዳን ቃል ዛሬም ቢሆን ህያው ነው ። መንጻታችንን መዳናችንን የሚወደው ጌታ ዛሬም ላንተም ላንቺም ለእኔም ይህንን ቃል ኪዳን እድርጎ ያውጅልናል የትኛውም ፍጥረት ከእጁ በሃጢአት ለምጽ ምክንያት እንዲለይ ስለማይፈልግ ለማንጻት ይጠራናል , ጥንቱን ሲመጣ ሊያነጻን ሊቀድሰን ነበር ። ከአዳም እስከ ክርስቶስ ከዘር በሚተላለፍ የውርስ ለምጽ ሁላችን ተመተን የጠላታችንን የዲያብሎስን ስድብና ንቀት እየሰማን እንሰቃይ በነበረበት የሞት ዘመን መዳናችንን የወደደው ጌታ ,ስጋ ተገለጠ የነፍስን በሽታ የሃጢአትን ለምጽ የሚያነጻውን ደሙን ስለሁላችን በቀራንዮ አባባይ አፈሰሰልን
ስጋውን ቆረሰልን ያን ጊዜ ሁላችን ለዘለአለም ነጻን ተቀደስን ስድባችን በመሰደቡ ጠፋልን ቁስላችን በቁሰሉ ተፈወሰልን ሞታችን በሞቱ ተሰረዘልን አንድ ጊዜ ሞቶ ለዘለአለም አደነን ።
      አሁንም ለዚህ ታጥቦ ለማይጸዳ አለም የጌታችን ጥሪ የመንጻት እና የመፈወስ ጥሪ ነው ደሙን የሚያሸንፍ ምንም ሃጢአት የለም ወንድሞቼና እህቶቼ ሰይጣን እግዚአብሔር በበደልህ{ሽ} ምክንያት ሊያጠፋህ ነው እያለበህሊና የሚናገረውን ሃሜት እንዳትሰሙ ሞታችንን ሳይሆን ዛሬም በህይወት መኖራችንን ይፈልጋል እወዳለሁ ንጻ ብቻ ሳይሆን እወድሃለሁ ንጻ ይለናል ንስሃ ስንገባ ስንመለስ እጆቹን ዘርግቶ ይቀበለናል ይራራልናል ይናፍቀናል ። አሜን ለዘለአለም በደሙ ያነጻን ቅድስናችን ንጽህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ለስሙ እና ለመንግስቱ  ይሁን።
       ቀሲስ ትዝታው ሳሙኤል
       

Popular posts from this blog

እንዴት እንጹም ?

አስገራሚው የፍቅር ታሪክ