ወንጌል /ግጥም/

                  ወንጌል

ወንጌል የምስራች ሰማያዊ ዜና
የልባችን ደስታ የነፍሳችን መና
ወንጌል ወንጀል ገዳይ
ወንጌል ብሩህ ፀሐይ
ጨለማ ገላጭ ነው የብርሃን ፀዳል
ወደ ሰማይ መውጫ የህይወት መሰላል
ከኢየሱስ አንደበት የተቀዳ ውሃ
ዘንቦ ማያባራ ደስታና ፍስሃ
ዶፍ ሆኖ ያራሰ የነፍስን በረሃ
የማይጠፋ ችቦ
ምስጋና ተከቦ
በሶምሶን ቀበሮ በሃዋርያት ጅራት
የታሰረ መብራት
የሃጥያት አውድማን የዲያብሎስን ክንድ
የበላ ነበልባል ያቃጠለ ሰደድ
የፍቅር አዋጅ ነው አዲስ ኪዳን መንገድ
ብሉይን ያስረጀ የይቅርታ ሰነድ
ትንቢትን ተርጉሞ ሚስጥሩን የፈታ
የእውነት ሰገነት የፍጥረት ከፍታ
ልደቱን ጥምቀቱን ስቅለት ትንሳኤውን
የኢየሱስን እርገት ዳግመኛ ምፅአቱን
ዘርዝሮ የነገረን ቸርነቱን ፍቅሩን
የመፃህፍት ራስ የኛም ልደት ቦታ
ወንጌል መስታወት ነው የአምላክ አንድምታ
የነፍስ አቡጊዳ
የህይወት ሃሌታ
የአዲስ ህይወት እድል
የአፍ መፍቻ ፊደል
እልፍ ቃል ነው ወንጌል ።
        ቀሲስ ትዝታው ሣሙኤል

Popular posts from this blog

እንዴት እንጹም ?

አስገራሚው የፍቅር ታሪክ