ጸሎት
ጸሎት
ጸሎት ማለት ከእግዚአብሄር ጋር መነጋገር ማለት ነው ። በጸሎት የምንፈልገውን ነገር ሁሉ ከጌታ ዘንድ መጠየቅ እና ማግኘት እንችላለን ። ከጸሃይ በታች ያለው ህይወታችን ጉድለት የበዛበት ሙሉ ሆኖ የማያውቅ ሙሉ መሆን የማይችል ቀዳዳ ነው ።በመሰረቱ ህይወት ጎዶሎ የሚሆነው ከምኞታችን አንጻር እንጂ ያለኝ ይበቃኛል ለሚል ሰው ጉድለቱን ሳይሆን ሁል ጊዜ የሚያየው ሙላቱን ነው ስለዚህ በምስጋና የተሞላ ማንነት አለው ። በመሰረቱ አብዝቶ ከሚጸልይ ይልቅ አብዝቶ የሚያመሰግን ሰው ብዙ በረከት ይቀበላል , መጽሃፍ ቅዱስ እንዳርጋገጠልን ጌታም እንዳስተማረው በቅድሚያ መንግስቱንና ጽድቁን ፈልጉ ሌላው ሁሉ ይጨመርላችሃል ማቴ 6፥33 እንዳለው እኛ ለቃሉ በተገዛ ማንነት የዘላለም መኖሪያ የሆነችውን ርስታችንን መንግስተ ሰማያትን ለመውረስ ጽድቅ በተባለው እውነት በኢየሱስ ክርስቶስ ለመዳን ብቻ ነው በጽኑ ማሰብ እና መፈለግ ያለብን ። በዚህ የጸሎት አቅጣጫ እስከዛሬ የዘለቅንበትን የጸሎት ህይወት ለመገምገም እንሞክራለን , በጉድለት የተሞላውን ማንነታችንንበቃኝ የማያውቀው ፍላጎታችንን እንዲሁም ልጛም የሌለው የምኞት ፈረሳችንን ከአንድ ምእራፍ ለማሳረፍ ትልቁ መፍትሄ ጸሎት ነው ። በጸሎት ፈጣሪን ተማጽነው ጠላታቸውን የረቱ ፣ ከመካንነት ነቀፋ ተገላግለው በልጅ የተባረኩ ፣ ከሰው ያሳነሳቸውን አንገታቸውን ያስደፋቸውን መብላት እየፈለጉ እንዳይበሉ ያደረጋቸውን የዘመናት በሽታ የተነቀለላቸው ፣ የዚህ አለም ገንዘብ ፍትሃዊ ስላልሆነ በለፉበት መጠን ሳይሆን ላባቸው ሚዛን ደፍቶ የበረከት ጥም እያንገበገባቸው በግፍ ወደሚገኝ ትርፍ ከመሄድ ያላቸውን እንዲባርክላቸው በጸሎት ለምነው ድህነትን ተገላግለው በሰማይና በምድር በረከቶች የተባረኩ ፣መንፈሳዊ ጸጋ ሽተው ጸጋ ያገኙ ፣በቢሮ የሚከናወን ጉዳያቸውን በክርስቶስ ፊት ዘርግተው የተከናወነላቸው ፣ የሞት ፍርድ ታውጆባቸው በእነርሱና በሞት መካከል ስንዝር ሲቀር በመለኮታዊ ጥበቡ ያመለጡ፣ በሃሰት ተከስሰው ፍርድ ቤት ቀርበው የእውነት አምላክ ሃሰትን ገልብጦ አርነት ያወጣቸው ፣ ወዘተ,,,,, ከቁጥር አቅም በላይ ናቸው ። መካን የነበረችው ሃና የብቸኝነት ህይወት ሲያንገበግባት ከዚሁ በላይ ደግሞ በጉድለታችን የማያዝኑልን የዚህ ዓለም ጨካኞች በስድብ ጥንካሬዋን ሲያደቁት በየቀኑ እየመጣች የእግዚአብሔርን ፊት በጸሎት መፈለግ ጀመረች እምባዋ እንደ ዝናብ በፊትዋላይ እየወረደ የልብ ጩኸት ጮኸች ለካህኑ ለኤሊ ይህንን የመሰለው ጸሎት የመጠጥ ውጤት የፈጠረው ስካር እንጂ በእምነት የሆነ ጸሎት አልመሰለውም ሴቲቱ ግን ጸሎት ወደሚሰማው አሰምታ ሄደች ። እግዚአብሔር አሰባት ለሁሉ ጊዜ አለው እንዳለ ሰሎሞን የሙላት ዘመን መጣላት የሰደባት ሁሉ አፉን በመደነቅ የሚዘጋበት ሃና ደግሞ ለምስጋና የምትጮህበት ጊዜ መጣ ጌታ ወንድ ልጅ ሰጣት ያውም ነቢይ በዘይት ቀንዱ ነገስታትን የሚቀባ እስራኤልን የሚመራ ታላቅ ሰው አስታቀፋት 1ኛ ሳሙ 1፥ 9-28 ።ውድ ክርስቲያኖች ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ምን ያህል ተቀባይነት እንዳለው አያችሁ ? ልጅ ማጣትን ያክል ከባድ ነገር የለም ይህን ጥያቄ የመለሰ አምላካችን የኛ ንም ጸሎት ሊሰማና ሊፈጽመው የታመነ ነው ።
ከጸሎት ጋር ተያይዘው የሚታዩ ልዩ ልዩ ነጥቦችን በዝርዝር እናያለን ምናልባትም የኔ ጸሎት ከቤቴ ጣርያ አያልፍም በሚል ተስፋመቁረጥ ውስጥ ያላችሁ ከዚህ ቀጠሎ በዝርዝር ከምናያቸው የህይወት ቃል እውነቶች ጋር ወቅታዊውን ማንነታችሁን በማነጻጸር ራሳችሁን እንድትመክሩ እጋብዛለሁ ፤አንድ ጸሎት ሙሉ ነው የሚባለው የሚቀጥሉትን ነጥቦች ሲያሟላ ነው
1ኛ) የእምነት ድፍረት
፤1ኛ ዮሃ 5፥14 <በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል ። እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን ከእርሱ የለመንነውን ልመና እንደተቀበለነው እናውቃለን ።> ይህ ቃል ለጸሎት ስትቆሙ ። ሁሌም ትዝ ይበላችሁ ስንጸልይ እየሰማን እንደሆነ እርግጠኞች ልንሆን ይገባል ከሰማን ደግሞ ያደርግልናል አንድ ማወቅ ያለብን ጉዳይ ግን ፀሎታችን ከጌታ ፈቃድ ጋር መስማማት አለበት ።
ያዕ 1፥8 <ሁለት ሃሳብ ላለው በመንገዱም ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው > በጥርጣሬ ሆነው ሳያምኑ የሚጸልዩ ሁሉ በከንቱ ጉንጭ ማልፋት እንጂ ውጤት ግን አይኖረውም ያለ እምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና ።ስለዚህ በታላቅ እምነት እንጸልይ ።ጌታ በወንጌል ለምኑ ይሰጣችሁማል ፈልጉ ታገኙማላችሁ መዝጊያውን አንዃኩ ይከፈትላችዃል ማቴ 7፥7 በማለት ታላቁን ኪዳን ስለገባልን ይህን መለኮታዊ ቃል አምነን እስከምንቀበል መትጋት አለብን ።እምነት የሌለው ጸሎት ቀለሃ የሌለው መሳርያ ማለት ለኢላማም ለአላማም የማይሆን ባዶ ነገር ማለት ነው ።
2ኛ) ፀሎታችን በምስጋና የታጀበ ይሁን
ምስጋና የሌለው እንዃን ጸሎት ንግግርም አይጣፍጥም የሰው ልጅ በሰራው ብቻ ሳይሆን ባልሰራውም ነገር ሲመሰገን ደስ ይለዋል ምስጋና የባህሪ ገንዘቡ የሆነው ፈጣሬ ዓለማት ልዑል እግዚአብሔር ደግሞ በእኛም ህይወት በሌሎችም ህይወት የፈጸመውን ታላቅ ማዳን በማስታወስ ቢመሰገን ያንስበታል እንጂ አይበዛበትም በዚህ ትጋታችን ደግሞ ደስ እናሰኘዋለን ። ወዳጆቼ ሆይ ምንም ጊዜ ስትጸልዩ በጸሎታችሁ መጀመሪያ እና መጨረሻ ባለውለታችን እግዚአብሄርን ማመስገን አትርሱ መድሃኒታችን ኢየሱስ ስለጸሎት ሲያስተምር« አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ {ይመስገን },,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,ሃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን » በመግቢያውና በመደምደሚያው በምስጋና የታጀበ ጸሎት አስጨብጧቸው ነበር ማቴ 6፥9-14።ፍጠረን ሳንለው ሰው አድርጎ የፈጠረንን ፣ በሞትንና በወደቅን ጊዜ ወርዶ ተወልዶ ያዳነንን በማይነገር ፍቅሩ የወደደንን ጌታ በጥሩ ቃላት በተከሸነ የጸሎት ምስጋና ልናከብረው ይገባዋል ትናንትና ያደረገልንን መልካም ውለታ በማስታወስ መሆን አለበት።
3ኛ) የምንለምነውን ማወቅ አለብን ።
ለፀሎት ቆመው ስለምን እንደሚፀልዩ እና ለምን በአምላካቸው ፊት እንደቆሙ በመዘንጋት ቃላት የሚጠፋባቸው ለፀሎት ቆመው በሐሳብ ማእበል የሚንገዳገዱ ምን ነበረ የጎደለኝ ብለው የጎደላቸውን ፍለጋ የሚወጡ ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም ።በጌታ ፊት የምናቀርበው አንድ ወይም ሁለት ጉዳይ ካለን እነርሱ እንዲፈፀሙልን "ጌታ ሆይ ዛሬ ባንተ ፊት የማቀርባቸው ያስጨነቁኝ እነዚህ ሁለት ነገሮች ናቸው " ብሎ በግልፅ በፅኑ ቃል መፀለይ አለብን ። አንዳድ ሰዎች ፀሎታቸው ተሰምቶ ተፈፅሞላቸው ካበቃ በኋላ ያንኑ ፀሎት ደጋግመው በእግዚአብሔር ፊት ያመጡታል ይህ ትልቅ አለማስተዋል ነው የምንለምነውን ካወቅን ከዚህም እንድናለን
ሌላው የመንለምነው የሚያጠፋን፣የማይጠቅመን፣ለፈተና የሚያጋልጠን፣የሚጎዳን እንዳይሆን አስበንበት አውቀነው ተዘጋጅተን ልንፀልይ ያስፈልጋል የያዕቆብ እና የዮሐንስ እናት ለልጆቿ ንግስናን ስትለምን ሳታውቀው ሞታቸውን በለመነችጊዜ ጌታ "የምትለምኑትን አታውቁም " ማቴ 20÷20—28 በማለት ገስፇታል ሳናውቀው ሞታችንን ወይም ውድቀታችንን እንዳንለምን ምን እንደምንፀልይ እንወቅ ። የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ሁላችንንም ያግዘን አሜን።
በጸሎታችንን የጎደለንን እንጠይቀዋለን አንዳንድ ራስ ወዳድ ጸሎተኞች ሁሌም በጌታ ፊት የሚቆሙት የራሳቸውን የግል ጉዳይ ብቻ ይዘው ነው መጥፎ ባይሆንም ግን በፀሎቱ ውስጥ የጎደለ ነገር አለው ክርስቲያን ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚያስብ የክርስቶስ ልብ ያለው ሰማያዊ ዜጋ ስለሆነ በጸሎቱ መሃል ስቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ስለአገልግሎት መከናወን ስለወንጌል መዳረስ ፣ስለ አገር ጉዳይ ስለ ሕዝባችን ጤና፣በረከት ፣ሰላም፣አንድነት ፣ ስለታመሙት፣ስለተሰደዱት፣ስለተራቡት፣ስለታሰሩት ,,,,,,,,,ወዘተ አስቦ መጸለይ አለበት ።ወደዚህ የጸሎት እድገት የምንመጣው ግን በጸሎታችን ለውጥ እንደሚመጣ ስናምን ነው ። የሰማን የሚሰማን ጌታ ይባረክ አሜን።
4ኛ) በትእግስት መጠበቅ
የትኛውም ተክል በተተከለበት ቀን ፍሬ አያፈራም ሁለት አመት ወይም ሶስት አመት መጠበቅ ግድ ይላል ,፤ አንዳንድ ክርስቲያኖች አስቸጋሪ የህይወት አጋጣሚ በደረሰባቸው እለት እግዚአብሔር ቤት መጥተው ያለቅሱና የጠፋባቸውን ከቤተክርስቲያን ተመልሰው ቤት ሲደርሱ ይፈልጉታል በዚህ ቅፅበት እግዚአብሔር መስራት ይችላል ብሎ ማመኑ ባይከፋም ቀጥሎ ተስፋን ማመንመኑ ነው ከባዱ ነገር መጽሃፈ ምሳሌ 27፥18 «በለሷን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፣ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል » በእኛ ጊዜና በጌታ ጊዜ መሃል
ሰፊ ልዩነት አለ ዛፉ ፍሬ እስኪያፈራ ፀሎታችን እስኪሰምር ጥቂት
ጊዜ መታገስ ይገባል ። አንድ እውነት ላካፍላችሁ 1/የለመንከውን ልመና ጌታ ወዲያው ከፈጸመልክ የሚጠቅምህን ሰጥቶሃል ዕምነትህን ሊያጸናው ፈልጎ ነው 2/የለመንከውን ካዘገየብህ ትዕግስት እያስተማረህ ነው 3/ጨርሶ ከከለከለህ ግን የምትሞትበት ወይም የምትጎዳበትን መንገድ እንደዘጋው ማወቅ ይኖርብሃል ። ወዳጆቼ ትዕግስት የእግዚአብሔር ባህሪ ነው ። እርሱ የዓለምን ሁሉ በደል እና ሃጢአት ፣የሚክደውን ፣የሚጠራጠረውን ፣ሁሉ ታግሶ ነው ይህን ሁሉ ዘመን ሁሉን የሚያኖረው ስለዚህ ተስፋ ሳንቆርጥ በትዕግስት በዕምነትና በምስጋና ሆነን እንጸልይ " አይነ ስውሩ ነው አሉ ከ30 አመታት በኋላ ነገ አይንህ ይበራል ሲባል ዛሬን እንዴት አድሬ? አለ ይባላል የዛሬዋን ሌሊት እንደ ትናንቱ በፅናት ካለፍነው ነገ መልካም ዜና ይዞ ይመጣል ሁሉም ጥሩ ይሆናል የትእግስት ሰው ኢዮብ ከብልፅግና በኋላ ያገኘው ድህነት ሕመም ጉስቁልና ቢያስመርረውም በጥርሱ ስጋውን ይዞ በልቡ ጌታን አንግሶ ዳግመኛ ጌታ ሲጎበኘው በእጥፍ በረከት ከብሯል ወገኖቼ ብንታገስ በእጥፍ እንባረካለን ። እግዚአብሔር ጸሎታችሁን ሁሉ ይስማችሁ ምኞታችሁን ሁሉ ከሃጢአት በቀር ይፈጽምላችሁ ።
ከቀሲስ ትዝታው ሳሙኤል