እውነት ኢየሱስ ነው።

         

                እውነት 2/ኢየሱስ የዘለዓለም እውነት ነው 

          እውነትን የሚተካው ብቸኛው ትርጉም በስጋ የተገለጠው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ጲላጦስ አይሁድ ክርስቶስን አሳልፈው በሰጡት ምሽት የዓለማችንን ትልቅ ጥያቄ ለጌታ አቀረበለት <እውነት ምንድነው?>ዮሐ 18፥38 ይህ ጥያቄ ዛሬም ክርስቶስን ለማያውቁ እና ለማያምኑ ሁሉ በደማቁ ተጽፎ ህሊናቸውን የሚሞግት ብርቱ ጥያቄ ነው ። ለእኛ ለምናምነው እና ለምንከተለው ወገኖቹ ግን የዘለአለም ጥያቄያችንን የመለሰው የዘላለም መልሳችን እና እውነታችን ኢየሱስ  ነው ።
         ወገኖቼ ዛሬ የጥያቄያችን መልስ አለማግኘት ብቻ ሳይሆን የሚያሳስበን ያገኘነው መልስ የቱን ያህል እውነተኛ ነው የሚለው ነው የሚያስጨንቀን ። ስለ እውነት ጠይቀን ሃሰት የተነገረን ስለእውነት ተከራክረን በሃሰት ቃል የተረታን በህዝብና በአህዛብ ፊት የተገለጠውን ሃቅ በተቀነባበረ ምስልና ድምጽ ብሎም የቃላት ውርጅብኝ ውሸት ነው የተባልን በአጠቃላይ እውነትን የተቀማን ሁሉ እውነታችን የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው ።
          ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም ዘሁል 23÷19 ይላል መፅሐፍ ማለትም ሰው ሃሰተኛ ጌታ እውነተኛ ነው ።አንዳንድ ሰዎች ከሃሰት ከክህደት ውጪ ስራ የሌላቸው ናቸው ይህንን ክፉ በሽታ ደግሞ እንደ ህይወት መመሪያ አድርገው ይኩራሩበታል "ካልዋሸህ አትኖርም" የሚለውን  የሰነፎች ተረት አታሞ እየመቱ ያዜሙታል በዚህ አለም ለመኖር ወገኖቼ መዋሸት ግዴታ አይደለም ።
       በትዳራችን ዋሽተን ፣ በልጆቻችን ዋሽተን ፣ ቤተሰብ ወላጆቻችንን ዋሽተን ፣ አሰሪዎቻችንን ዋሽተን 
ለገንዘብ ፣ ለዝና፣ለምድራዊ ክብር፣ ለሁሉ ነግር ዋሽተን አይሆንም እነዚህ የህይወት ስኬቶች እኮ በእውነት ሆነን በክርስቶስ ሆነን ማግኘት እንችላለን ። ሃሰተኛ ሰው ክርስቶስ በህይወቱ የለም ምክንያቱም ክርስቶስ እውነት ስለሆነ ። ሃሰተኛ ሰው መጀመሪያ የገዛ ራሱን ይዋሻል ሃጢአተኛ እንደሆነ አያወቀ ራሱን ይዋሽና እኔ ፃድቅ ነኝ ተንኮለኛነቱን ይክድና የዋህ ቅን ነኝ ይላል የሌለውን  አለኝ ያለበትን የለብኝም ይላል ራሱን የዋሸ ደግሞ ሰዎችን ቀጥሎ እግዚአብሄርን ይክዳል ከዚህ አይነት የተሸነፈ ህይወት ጌታ ይጠብቀን የገቡበትንም በመገላገያው ይገላግልልን ። ሃሰተኛ የሃሰት አባት የተባለው ዲያብሎስ ነው የሚገርመው ሰዎች ሃሰታቸውን አሳድገው በክርስቶስ እውነት ፣ በቃሉ ላይ እየዋሹ ይገኛሉ ይህ ደግሞ የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰው ቦታ ቆሞ ባያችሁ ጊዜ አንባቢው ያስተውል እንዳለው የፍፃሜው ዘመን የጥፋት ምልክት ነው ። 
          ሰውየው አሉ ከሰው ቤት ሊሰርቅ ይገባና በፍጥነት ሲያማትር አንድ መፅሃፍ ጠረጴዛው ላይ  ያገኛል መፅሐፍ ቅዱሱን ይዞ ሰዎቹ ሳይደርሱበት ፈትለክ ሲል ከበስተኋላው ሌባ ሌባ እያለ በዛ ያለ ሰው ተከተለው ድንገት በፍርሃት ሲወራጭ መፅሃፉ ከእጁ ይወድቃል ሲወድቅ የተገለጠው ዘፀ 20 አሰርቱ ትእዛዛት አይኑ ያረፈው አትስረቅ
የሚለው ህግ ላይ ተናደደና መውደቅ ሲያንስብህ ነው ብሎ ትቶት ሸመጠጠ የጣለው እውነት ስለነገረው ነው  ። ብዙዎች ጨለማቸውን የገለጠውን ብርሃን ይሸሹታል ፣ ስህተታቸውን የነገራቸውን ጓደኛ ይለዩታል ። እውነት የሆነውን ጌታ እንከተል ያም እውነት ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ያደርሰናል። እውነት ጌጣችን ውበታችን ይሁን 
ፅድቅ ማለት እውነት ማለት ነው ለእውነት የሞቱትን ዛሬ ፃድቃን እውነተኞች እንላቸዋለን ለእውነት ከኖርን ሁላችን ፃድቃን ነን። "እግዚአብሔር እውነተኞችን ይፈልጋል ትእቢተኞችንም ፈፅሞ ይበቀላቸዋል" መዝ 30÷23።
     ቀሲስ ትዝታው ሣሙኤል

Popular posts from this blog

እንዴት እንጹም ?

አስገራሚው የፍቅር ታሪክ