ሕይወት ኢየሱስ ነው ።
ሕይወት ኢየሱስ ነው ። <<ሕይወት ተገለጠ አይተንማል >>1ኛ ዮሐ 1፥2 በሞት ተሸንፎ ለወደቀው አለም የተገለጠው ሕይወት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ኢየሱስ ሕይወት ብቻ ሳይሆን የዘለአለም ሕይወት ነው ። 1ኛ ዮሐ 5፥20 በጥንታዊው ሰው በአዳምና በአጋሩ በሔዋን አለመታዘዝ ምክንያት ሕይወት የውሃ ሽታ ሆኖ የገነት ደጃፎች ተከርችመው የሲኦል መግቢያ ወለል ብሎ ተከፍቶ ከአቤል ግድያ እስከ ክርስቶስ መስዋእትነት ድረስ እጅግ ብዙ ነፍሳትን ውጧል ሞት በሃጢአት ምክንያት የመጣብን የበደላችን ዋጋ ስለሆነ ከህይወት ተለይተን ኖረናል ። የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ እንዳለው 1ኛ ዮሐ 3፥8 ጌታችን የመጣው በዲያብሎስ ተንኮል የተተበተበውን የሞት መረብ በጣጥሶ ነጻነት ሊሰጠን ነው ። ስለዚህ ህይወት ሲገለጥ ሞት መግቢያ መውጫ ጠፋው በመስቀል ላይ በደም ታነቀ፣ ታሰረ፣ኢየሱስ ጠላታችንን በመስቀሉ ጠርቆ አስሮ ነፍሱን ከስጋው በገዛ ስልጣኑ ለይቶ በአካለ ነፍስ በግርማ ወደ ሲኦል ወርዶ ለዘመናት በባርነት የተገዛውን አዳምን ከልጅ ልጆቹ ጋር ነጻ አወጣው ። ሲኦል ባዶ ቀረ ክርስቶስ ከበረ። ያን ጊዜ የዘለአለም ሕይወት ለሰዎች ሁሉ ተመልሶ ተሰጠን ። ውድ ክርስቲያኖች ይህ ውድ ዋጋ የህይወት መሷእትነት የተከፈለው ለእኔም ለአንተም ለአንቺም መሆኑን አምነን ለክርስቶስ ፍቅር ልንገዛ ልናመልከው ልናመሰግነው ይገባል ። ዮሐ 3፥16 በእርሱ የሚያምን ሁሉ...